ትግራይ ክልል ገብተው ዘገባ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው አለም አቀፍ ሚድያዎች አሉ?
“መንግሥት ቢቢሲ እና ሮይተርስን ጨምሮ 7 ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ትግራይ ክልል ገብተው ስላለው ሁኔታ መዘገብ እንዲችሉ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ” የሚል ዘገባ የመንግስት ሚድያዎች ዛሬ ማምሻውን አስነብበዋል።
በዘገባዎቹ መሰረት ከሁለቱ የሚዲያ ተቋማት በተጨማሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ በክልሉ ስላለው ሁኔታ መዘገብ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው የሚድያ ተቋማት ኤኤፍፒ፣ አልጀዚራ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ፍራንስ 24 እና ፋይናንሺያል ታይምስ ናቸው።
ኢትዮጵያ ቼክ አመሻሹን ማረጋገጥ እንደቻለው የኤኤፍፒ፣ ፍራንስ 24 እና ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጠኞች ፍቃድ አግኝተው ወደ ክልሉ ዛሬ ጠዋት ተጉዘዋል። የተቀሩት እና በመንግስት ሚድያዎች ላይ የተጠቀሱት አለም አቀፍ ሚድያዎች ሁኔታ ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም። ለሌሎች አለም አቀፍ ሚድያዎች የሚሰሩ ጋዜጠኞች ደግሞ ስለ ጉዞው ጭራሽ መረጃ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ እንደቻለው ይህን ወደ ትግራይ ለዘገባ የተዘጋጀ ጉዞ እያስተባበሩ የሚገኙት የብሮድካስት ባለስልጣን፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው።
በርካታ መንግስታት እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ለወራት የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ክልልን ለሰብአዊ ድርጅቶች እና ለጋዜጠኞች ክፍት እንዲያደርጉ ሲጎተጉቱ ቆይተዋል።
የሰብአዊ ድርጅቶች አሁንም በርካታ ስፍራዎችን መድረስ እንዳልቻሉ እየገለፁ ይገኛሉ፣ መንግስት በበኩሉ ለ135 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትግራይ ክልል ገብተው የሰብአዊ ድጋፍ ሂደቱን እንዲዘግቡና እንዲያግዙ ፈቃድ ሰጥቻለሁ ብሏል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::