ይህ ምስል አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በጎርጎራ የሚሰራውን ሪዞርት ያሳያል?

“የኔታ ትዩብ” የተባለው ኦንላይን ሚድያ ከሁለት ቀን በፊት አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በጎርጎራ የሚሰራው ነው ያለውን ምስል የፌስቡክ ገፁ ላይ ለ 1.7 ሚልዮን ገደማ ተከታዮቹ አጋርቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ጎርጎራ ላይ ይሰራል የተባለው ሆቴል “JW Marriott Hotel Sanya Dadonghai Bay” በሚል ስም ቻይና ውስጥ የሚገኝ ሆቴል ነው።  ሆቴሉ ሀይናን ግዛት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ነው።

ኢትዮጵያ ቼክ ተጨማሪ መረጃ ከሀይሌ ሆቴል እና ሪዞርት ድርጅት የጠየቀ ሲሆን ድርጅቱ የተባለውን ምስል እንደማያውቀው ተናግሯል። “እስካሁን በዲዛይንም ሆነ በእቅድ ደረጃ ይህ ነው የሚባል ነገር የለም፣ ጎርጎራ ላይ በሚከናወናው ልማት ላይ ሀይሌ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ቀድሞ ተናግሯል። ምስሎችን እየለጠፉ ይሄ ነው የሚሉትን ግን አናውቃቸውም” ብለው መልስ ሰጥተዋል።

ሀገራዊ ፕሮጀክት የሚካሄድባት ጎርጎራ በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኝ ታሪካዊ የወደብ ከተማ ናት። ጎጃም እና ጎንደርን የምታገናኝ ከመሆኑ ባሻገር፣  ዓሣ ማጥመድ የሚዘወተርባት እና ሸቀጦች የሚተላለፉባት ከተማ ናት።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::