በመረጃ ማጣራት ዙርያ የሚሰጡ ስልጠናዎች አስፈላጊነት!
ኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ የካቲት 8 እና ነገ የካቲት 9፣ 2013 ሀያ (20) ለሚሆኑ ጋዜጠኞች በመረጃ ማጣራት ዙርያ ስልጠና ይሰጣል። አስሩ ጋዜጠኞች ከአዲስ አበባ የተውጣጡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አስሩ ደግሞ ከመዲናዋ ውጪ የሚመጡ ይሆናሉ። በፆታ ስብጥር ሲታይ ደግሞ ሴቶች እና ወንዶች ግማሽ፣ ግማሽ ሆነው ይካፈላሉ።
ኢትዮጵያ ቼክ በመረጃ ማጣራት ዙርያ ስልጠና ሲያዘጋጅ ይህ ሶስተኛው ሲሆን ለሁለት ቀናት ፊት-ለፊት በሚካሄድ ሂደት የሚከናወን ይሆናል።
ጋዜጠኞች መረጃ በማቅረብ ግንባር ቀደም ከመሆናቸው አንፃር መረጃን በማጣራት ዙርያም ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ እንገነዘባለን። አንዳንድ የዘርፉ ፀሀፊዎች እንደሚሉት “መረጃ ማጣራት ለጋዜጠኞች አንድ አዲስ ተጨማሪ የስራ ድርሻ ሆኗል።”
እንደ ቀደመው ግዜ መረጃ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካላት የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎችን ማጋለጥም የጋዜጠኞች እና የመረጃ አጣሪዎች ሀላፊነት እየሆነ ይገኛል። ይህን ስራ ለማከናወን ደግሞ ተገቢው ስልጠና እና ለስራው የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ማዳበር ይገባቸዋል።
በርካታ ዜና ተከታታዮች የሚቀርብላቸውን መረጃ ከመውሰድ ውጪ ሲሞግቱ እና ሲያሰላስሉ አይታዩም፣ ይህም ለሀሰተኛ መረጃ ሰለባ ያደርጋቸዋል። ይህ በራሱ ዜናዎችን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ስራቸው ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና የሚያቀርቡት መረጃ ትክክለኛ እንዲሆን እንዲጥሩ ጥሩ ምክንያት ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የሚድያ አረዳድ እና አጠቃቀም አነስተኛ በሆነባቸው ሀገራት የጋዜጠኞች የመረጃ ማጣራት ስራ ከፍተኛ ድርሻ ሊይዝ ይገባል፣ ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ቼክ ተከታታይ ስልጠናዎችን ወደፊትም ያዘጋጃል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::