የሰኞ መልዕክት

መረጃ የማጣራት ስራ በገለልተኛ ተቋማት እና በሚዲያዎች መከወኑ የተለመደ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግስታት የራሳቸውን መረጃ አጣሪ ተቋማት በመመስረት መረጃ ወደ ማጣራት ስራ ሲቀላቀሉ በስፋት ይታያል።
የሜክሲኮ ፕሬዝደንት ሎፔዝ ኦብራዶር “Verificado Notimex” የተባለ የመረጃ አጣሪ ተቋም የመሰረቱ ሲሆን የህንድ ፕሬስ ኢንፎርሜሽን ቢሮ (Press Information Bureau) የመረጃ አጣሪ መምሪያ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሂንዱ ታይምስ ጋዜጣ በቅርቡ አስነብቧል። በእስያ እና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ በርከት ያሉ አገራትም ተመሳሳይ መንግስታዊ የመረጃ አጣሪ ተቋማት ተመስርተዋል ወይንም ለመመስረት በሂደት ላይ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያም በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኃላ የፌዴራል መንግስት “የአስቸኋይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ” በሚል ስያሜ የትዊተር እና የፌስቡክ ገጾችን ከፍቷል።
“የአስቸኋይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ” ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በመገናኛ ብዙሐን የሚሰራጩ መረጃዎችን የማንጠር ስራ ለመከወን እንደተቋቋመ ስያሜው ፍንጭ ይሰጣል። ባለፉት ሳምንታትም በተለይ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐን የሚያወጧቸውን ዘገባወች ለማረም ሙከራ ሲያደርግ ተስተውሏል።
መንግስታት መረጃን ወደማጣራት የገቡበት ድርጊት ‘የጥቅም ግጭት (conflict of interest) አይፈጥርም ወይ?” የሚለው ጥያቄ በመነሳት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም ይህ የመንግስታት ድርጊት መረጃ በማጣራት ስራ ሊተገበሩ የሚገባቸውን መርሆች የመጣስ እድሉ የሰፋ ስለመሆኑ ብዙዎች ይከራከራሉ። ለምሳሌ በርካታ የመረጃ አጣሪ ተቋማትን በአባልነት የያዘው አለማቀፉ የመረጃ አጣሪዎች ትስስር (International Fact-Checking Network) በመረጃ ማጣራት ሂደት መተግበር አለባቸው ከሚላቸው 5 መርሆች በቁጥር አንድ የተቀመጠው ‘ከወገንተኝነት እና አድሎ ነጻ መሆን’ በመንግስት የመረጃ አጣሪዎች የመተግበሩ ጉዳይ አጠያያቂ ነው።
ከዚህ አልፎም መንግስታት በመረጃ ማጣራት ስራ ላይ መሰማራታቸው ህብረተሰቡ በመረጃ አጣሪ ተቋማት ላይ ያለውን እምነት ይሸረሽራል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ይህ እንዳለ ሆኑ ሚድያዎች እና ሌሎች ገለልተኛ ተቋማት ይህን መረጃ የማጣራት ስራ ቢሰሩ ውጤቱ ጥሩ እንደሆነ አለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያስረዳሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::