በርሃብ አድማ ላይ የቆዩ እስረኞች አድማቸውን አቋርጠዋል?
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በርሃብ አድማ ላይ የቆዩ እስረኞች አድማቸውን ማቋረጣቸውን በጻፉት አንድ ደብዳቤ ገልጸዋል። አምባሳደር ፍጹም እስረኞቹ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምና ማግኘት እንደሚችሉ፣ ህክምና አስፈልጓቸው የነበሩ የርሃብ አድማ ተሳታፊ እስረኞችም መታከማቸውንና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ፍጹም ይህን የገለጹት የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ኢልሀም ኦማር እ.አ.አ ፌብሯሪ 19 ቀን 2021 ዓ.ም ለሰጡት መግለጫ ምላሽ በጻፉበት ደብዳቤ ነው። ኢልሀም በመግለጫቸው አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ ያሏቸው እስረኞች ሁኔታ እንዳሳሰባቸው እና የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩርት እንዲሰጥ አሳስበው ነበር።
ኢትዮጵያ ቼክ በርሃብ አድማ ላይ የቆዩ እስረኞች አድማውን ስለማቋረጣቸው ለማወቅ ከእነ አቶ በቀለ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑትን አቶ ቱሊ ባይሳን አነጋግሯል። የህግ ጠበቃው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ደንበኞቻቸውን በትናንትናው ዕለት ከጠዋቱ 3- 5 ሰዐት መጎብኘታቸውን ገልጸው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጃዋር ሲራጅ ሞሐመድ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ የርሃብ አድማውን መቀጠላቸውን ተናግረዋል። አቶ ሸምሰዲን ጠሃን ጨምሮ ሌሎች አስራ ስድስት እስረኞች ግን የርሃብ አድማውን አቋርጠዋል ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።
ጠበቃ ቱሊ ለኢትዮጵያ ቼክ እንዳስረዱት ከሀያ አምስት ቀናት በፊት የርሃብ አድማውን የጀመሩት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጀዋር ሲራጅ ሞሐመድ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ሲሆኑ በሂደት አቶ ደጀኔ ጣፋን ጨምሮ አስራ ስድስት ሰዎች አድማውን ተቀላቅለው ነበር። ከአስር እና አስራ አንድ ቀናት በኃላ በርሃብ አድማው ተሳታፊዎች ላይ እራስን መሳት እና መውደቅን ጨምሮ ጉዳት እየደረሰ በመምጣቱ በሽማግሌዎች አግባቢነት አስራ ስድስት ሰዎች አድማውን እንዲያቋርጡ ሆነዋል።
የህክምና አገልግሎትን በተመለከተ ደንበኞቻቸው በግል ሃኪሞቻቸው ለመታከም ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ፍርድ ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ትዕዛዝ ቢሰጥም “ጠቅላይ አቃቤ ህግ የመንግስት ሆስፒታል ካልሆነ መታከም የለባቸውም በማለቱ የህክምና አገልግሎት እያገኙ አይደለም” ሲሉ ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በደንበኞቻቸው ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።
በትናትናው ዕለት ደንበኞቻቸውን በጎበኙበት ወቅት በተለይ አቶ በቀለ ተዳክመው ማየታቸውን የገለጹት ጠበቃው “አቶ በቀለ መነሳት አልቻለም። ወጥቶም ሊያናግረን አልቻለም። አቶ ጃዋር እና አቶ ሀምዛ ትንሽ ትንሽ ይናገራሉ። አቶ በቀለ መናገር አይችሉም። ማንም ሰው ይህን ሄዶ ማረጋገጥ ይችላል” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ ደንበኞቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የታሳሪዎች ቤተሰብ አባልም “የርሀብ አድማው አልቆመም፣ አቁመዋል የሚለው መረጃ ከየት እንደመጣ አላውቅም” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።
እነ አቶ በቀለ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ መሆን ጠበቆቻቸው በተለያየ ጊዜ ለሚዲያ መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ‘Oromo Political Prisoners Defence Team’ የተባለ ቡድን ባወጣው መግለጫ አምባሳደር ፍጹም እስረኞችን በተመለከተ የጻፉትን ደብዳቤ “አሳሳች እና ትክክል ያልሆነ ነው” ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
ስለዚህ የተወሰኑ የርሀብ አድማ ሲያረጉ የነበሩ ሰዎች አድማቸውን ቢያቆሙም የተወሰኑት እስካሁን በአድማቸው እንደቀጠሉ ነው። ይህም የአምባሳደሩን መረጃ “ቅይጥ- ግማሽ እውነት፣ ግማሽ ሀሰት” ያደርገዋል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::