በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ታግዶ የነበረ ገንዘብ በጆ ባይደን አስተዳደር አሁን ላይ ለኢትዮጵያ እንዲለቀቅ ተደርጓል?
የትራምፕ አስተዳደር በህዳሴ ግድብ ዙርያ በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መሀል ባለው አለመግባባት ምክንያት ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ገንዘብ ላይ አግዶት የነበረውን ገንዘብ የባይደን አስተዳደር አሁን ላይ እንደመለሰው የሚገልፁ ፅሁፎች ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየወጡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ ማረጋገጥ እንደቻለው አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር 272 ሚልዮን ዶላር የሚሆነውን እና በቀድሞው አስተዳደር ታግዶ የነበረው ገንዘብ ከህዳሴ ግድብ ጋር እንዳይያያዝ ወስኗል። ይህም እገዳው ከዚህ በሗላ ከግድቡ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ያመላከተ ሆኗል።
ይሁንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ዛሬ እንዳመላከተው ይህ የገንዘብ መጠን አሁኑኑ ለኢትዮጵያ ይለቀቃል ማለት አይደለም ያለ ሲሆን ይህም “ከቅርብ ግዜ የሀገሪቱ ክስተቶች” ጋር ያያዛል ብሏል። ስለዚህ ይህ ገንዘብ አሁንም በአዲሱ የአሜሪካ መንግስት እንዲያዝ መደረጉ እና አሁን ላይ ምክንያቱ ደግሞ በትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር መያያዙ ታውቋል።
ስለዚህ በአጭሩ በቀድሞው የአሜሪካ መንግስት በህዳሴ ግድብ ምክንያት ታግዶ የነበረ ገንዘብ አሁንም በትግራይ ግጭት ምክንያት ታግዶ እንዲቆይ ተወስኗል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረውን ይህ 272 ሚልዮን ዶላር ገደማ መስከረም ወር ላይ ያገደችው በወቅቱ ፕሬዝደንት በነበሩት ትራምፕ ትእዛዝ እና አመራር መሆኑን ስቴት ዲፓርትመንት ያሉ ምንጮች በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ስታደርግ የነበረው ውይይት ውጤት አልባ መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያን ተጠያቂ በማድረግ እንደሆነ ተጠቅሶ ነበር፣ በተጨማሪም “ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡን ሙሌት በማከናወኗ” ነው ተብሎ ተገልፆ ነበር።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::