ትናንት በአራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ዙርያ በተሰራው ዘገባ ፋና እና ኢቢሲ የሚጋጭ እና የተለያየ መረጃ አቅርበዋል፣ ትክክለኛው የቱ ይሆን?

ትናንት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ፋና) እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙ አራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የወንጀል ምርመራ ማቋረጡን አስታወቀ የሚል ዘገባ ሰርተዋል።

ፋና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን በምንጭነት በመጠቀም የጦር መኮንኖቹ የጊዜ ቀጠሮ ይቋረጥ እንጂ ተጠርጣሪዎቹ ነፃ ናቸው አለመባሉን እንዲሁም ከእስር አለመፈታታቸውን አስነብቧል።

ኢቢሲ በበኩሉ በጦር መኮንኖቹ ላይ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ቼክ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮን ትክክለኛ ውሳኔ ለማወቅ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴን ያነጋገረ ሲሆን “የፋና ዘገባ የተሳሳተ ነው” የሚል ምላሽ አግኝቷል። ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ የምርመራ ቢሮው ትክክለኛ ውሳኔ በኢቢሲ ዘገባ መንጸባረቁንም ጨምረው ተናግረዋል።

በኢቢሲ ዘገባ መሰረት ምርመራቸው እንዲቋረጥ እና ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት የጦር መኮንኖች ሜ/ጀ መሀመድ ኢሻ ዘይኑ ትኩእ፣ ብ/ጀ ሙሉጌታ በርሄ ይልማ፣ ኮ/ል ገ/እግዚአብሔር ገ/ሚካኤል እና ኮ/ል ገ/ዋህድ ኃይሉ መሸሻ ናቸው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::