አክቲቪስቶች፣ የመንግስት አካላት እና የተቃዋሚ አካላት የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ከ1-3 ደረጃ የያዙበት ውጤት ምን ይነግረናል?
ኢትዮጵያ ቼክ ከቀናት በፊት “በአንፃራዊነት የሀሰተኛ መረጃዎችን በብዛት ሲያሰራጩ የትኞቹን ተመልክተዋል?” የሚል ጥያቄ ለተከታዮቹ ቴሌግራም ላይ አቅርቦ ነበር፣ ከአንድ በላይ መምረጥ እንዲቻልም ክፍት ተደርጎ ነበር።
በውጤቱም 77 ፐርሰንቱ አክቲቪስቶች፣ 42 ፐርሰንቱ የመንግስት አካላት፣ 41 ፐርሰንቱ የተቃዋሚ አካላት፣ በተመሳሳይ 41 ፐርሰንቱ ጦማሪዎች እንዲሁም 36 ፐርሰንቱ ሚድያዎች እና ጋዜጠኞች በአንፃራዊነት የሀሰተኛ መረጃዎችን በብዛት ሲያሰራጩ ማየታቸውን ጠቁመዋል። በአጠቃላይ 2,209 ድምፅ ቴሌግራም ላይ ተሰጥቷል።
ይህ እንግዲህ በህብረተሰቡ ዘንድ በሀሰተኛ መረጃዎች ምንጮች ዙርያ ያለውን አስተሳሰብ በወፍ-ዘለል ያመላከተ ሲሆን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ለሚሰራው ስራም የትኩረት አቅጣጫ በጨረፍታ ያመላከተ ነው። እኛም ይህንን ጉዳይ በአጭሩ እንዳስሰው።
አክቲቪስቶች!
በአለም ዙርያ በአክቲቪዝም ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች ስራቸውን ለማከናወን የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ። ከነዚህም መሀል የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻዎችን ማስተባበር፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተገኘው አጋጣሚ መሞገት እንዲሁም ስልቶችን ነድፎ ተባባሪዎቻቸውን ለስራ ማነሳሳት ይገኙበታል። እንዳለመታደል ሆኖ በሀገራችን የአክቲቪዝም ስራ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተተወ ይመስል በሌሎች መስኮች ብዙም ሲተገበር አይታይም። ሁሉም ባይባሉም በፖለቲካው ላይ የሚሳተፉት አክቲቪስቶችም የሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ በተራ ስድድብ እና ንትርክ ግዜ በመፍጀት እና የተቃራኒ ሀሳብ ያላቸውን በመዝለፍ እና ስም በማጠልሸት ላይ ተጠምደው ይታያሉ። ይህ ጉዳይ በጣም ግልፅ እየሆኑ ከመምጣቱ አንፃር 77 ፐርሰንት ድምፅ ሰጪዎች አክቲቪስቶች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ድምፅ ሰጥተዋል።
የመንግስት አካላት!
የመንግስት አካላት ሀገርን ከማስተዳደር በተጨማሪ ተገቢ መረጃዎችን በወቅቱ ለህዝብ ማድረስ ሀላፊነታቸውም፣ ግዴታቸውም ነው። ልክ እንደ አክቲቪስቶች ሁሉ በደፈናው መናገር ባይቻልም የመንግስት አካላት የሀሰተኛ መረጃ ምንጮች እየሆኑ እየመጡ እንደሆነ ይታያል። ይህ አደገኛ አዝማሚያ ሲሆን የሀሰት መረጃዎች ቀስ በቀስ ሲጋለጡ እና እውነታው ሲወጣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንዲቀንስ፣ ብሎም እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቀነስ ህግ ያወጣ አካል መልሶ ህጉን ሲጥሰው ማየትም አደገኛ አካሄድ (precedent) ያስከትላል። 42 ፐርሰንት የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች የመንግስት አካላት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ድምፅ ሰጥተዋል።
የተቃዋሚ አካላት!
በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉትም እንዲሁ በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ተጠምደው ይታያሉ። በፖለቲካ ሜዳው ማሳካት ያልቻሉትን የሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ለማግኘት የሚሞክሩ እንዳሉ የእለት ተእለት ትእይንት ሆኗል። አሁንም ሁሉንም በደፈናው ማለት ባይቻልም የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አመራሮቻቸው እንዲሁም አባሎቻቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም ሀሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን ሲለቁ በብዛት ይታያል። 41 ፐርሰንት የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች የተቃዋሚ አካላት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ድምፅ ሰጥተዋል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::