ኦፌኮ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በምርጫው እንደማይሳተፍ ተናግሯል?

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል።
ኦፌኮ በመግለጫው “…ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ስናሳውቅ እንደቆየነው ሁሉ ከፌድራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ታዛቢ፣ ተወዳዳሪና አስተባባሪ ሊሆኑ የሚችሉ አመራርና አባሎቻችን ታስረውና ከማዕከላዊ ጽ/ቤት ውጭ ያሉ አብዛኛው ቢሮዎቻችን ተዘግተው ባሉበት ሁኔታ ውስጥ በምርጫው ለመሳተፍ እጅግ አስቸጋሪ ይሆንብናል” የሚል ዐረፍተ ነገር ተጠቅሟል።
መግለጫው በተለያዩ ሚዲያዎች የተሰራጨ ሲሆን በርካታ ተከታዮች ያሉት አዲስ ስታንዳርድ ኦፌኮ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በምርጫው እንደማይሳተፍ እንደገለፀ የሚጠቁም ትርጉም ያለው ዜና በትዊተር ገጹ አጋርቶ ነበር። ኢትዮጵያ ቼክ ዜናው ተዛብቶ የተተረጎመ መሆኑን መግለጫውን በመመልከት እና የፓርቲውን ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲናን በማናገር አረጋግጧል።
ኦፌኮ መግለጫውን በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ብቻ ማውጣቱን ፕ/ር መረራ ለኢትዮጵያ ቼክ የገለጹ ሲሆን፣ የመግለጫው መልዕክት “ግልጽ” መሆኑን ተናግረዋል።
ማምሻውን አዲስ ስታንዳርድ ዜናው ላይ ማስተካከያውን አድርጓል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::